አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየተከናወነ ያለው የሰላም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ገለጹ።
የሃይማኖት ተቋማት ሚና ለሳላም ግንባታና ለእርቅ በሚል መሪ ሐሳብ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈና ሁለት ቀናት የሚቆይ የሰላም ኮንፈረንስ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ፥ በክልሉ ህብረተሰቡን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተከናወኑ የሰላም ግንባታ ሥራዎች ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተጀመረው የሰላም ግንባታ ሥራ በቀጣይም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፥ በዚህ ሂደት የሃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።