አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ እየደገፈ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርትን የማስፋት ስራ እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
ሚኒስትሩ በቡራዩ የሚገኘውን የፕራይም ቴክ ኢንጅነሪግ ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ከዚህ ቀደም ብረቶችንና እንጨቶችን በሚፈለገው ቅርጽ ለመቁረጥ የምንጠቀማቸው ማሽኖች በእጅ የሚሰሩ በመሆናቸው ጉልበትና ጊዜን ይወስዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ የፕራይም ቴክ ኢንጅነሪግ ፋብሪካ የሚያመርታቸው የሲኤንሲ ማሽኖች ዓለም የደረሰበትን ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተላበሱና በኮምፒዩተር የሚታገዙ መሆናቸው ስራውን ቀላል፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንደሚያደርገው መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
ፋብሪካው ገቢ ምርትን የመተካት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው÷ የተወሰኑ ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት የምርቶቻቸውን ዲዛይን ማውጣት፣ መቁረጥና የመሳሰሉ ስራዎች ተደምረው 75 በመቶ የሚሆኑ ስራዎች በሀገር ውስጥ ግብዓትና በኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሚከናወን መሆኑን አንስተዋል።