Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከጌትስ ፋውንዴሽን የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት÷ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የግብርና ዘርፍን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ለአብነትም የኩታ-ገጠም ልማትን ማስፋፋት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማጠናከርና ዘርፉ በቴክኖሎጂ እንዲዘምን ለማድረግ መሰራቱን አንስተዋል፡፡

በግብርና ኢንቨስትመንትና በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት የግብርና ልማት ሥራዎች ምርታማነትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የጌትስ ፋውንዴሽን ሃላፊዎች በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

Exit mobile version