አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና ጸጥታን ማስፈን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡
በተለይም የአፍሪካ ኅብረት በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እያደረገ ያለው የማሸማገል ጥረት በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ ህብረት እየተከናወኑ በሚገኙ ተቋማዊ የማሻሻያ ሥራዎች ዙሪያ መምከራቸውን የህብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ ÷ መሃሙድ አሊ ዩሱፍ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እያሳዩት ላለው የአመራር ቁርጠኝነት እና ባለ ብዙ ወገን ትብብር አመስግነዋል፡፡
መሃሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ እያበረከተችው ላለው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡