Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሜክሲኮ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር አሊሃንድሮ ኢስቲቪል ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት በፊት የዝናብ ጥገኛ የነበረውን የስንዴ ልማት በአሁኑ ወቅት በመስኖ በስፋት እያመረተች መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአርሶ አደሩን የሜካናይዜሽን ፍላጎት ለማሟላት የሜክሲኮ ባለሃብቶች ተሰማርተው ምርቶችን በማቀነባበርና ግብርናውን በማዘመን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሜክሲኮ በበቆሎና ስንዴ ማሻሻያ ማዕከል የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር አሊሃንድሮ ኢስቲቪል በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ሜክሲኮ ግብርናን በማዘመንና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ያላትን ከፍተኛ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሜክሲኮ በትብብር ለሚያከናውኗቸው የግብርና ሥራዎች በቅርቡ የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ መገለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version