አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒሰትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘውን የቃሊቲ ዘመናዊ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት ሞዴል መናኸሪያን ጎብኝተዋል፡፡
መናኸሪያው በሰዓት 120 አውቶቡሶችንና 7 ሺህ 200 ተሳፋሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በውስጡ ካፍቴሪያዎች፣ ሱቆች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የመመገቢያ ስፍራዎች፣ ከ1ሺህ 130 በላይ የማረፊያ ወንበሮችና የታክሲ ተርሚናል የተዘጋጀለት ማዕከል ነው ተብሏል።
የመናኸሪያው ግንባታ በ3 ነጥብ 9 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፥ በውስጡ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል ባለ አራት ወለል ህንፃ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።