Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብርቱካን ተመስገንን ጨምሮ በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብርቱካን ተመስገንን ጨምሮ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች ላይ ፍርድ ቤት ለፖሊሲ ተጨማሪ 12 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ብርቱካን ተመስገንን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙኃን ከተላለፈው ሐሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ጋር በተያያዘ፤ ብርቱካን ተመስገን፣ ነብዩ ጥዑመልሳን የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ፣ ታሪኩ ኃይሌ የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ፣ ደረጀ ሉቃሌ፣ ኅሊና ታረቀኝ፣ ንጥር ደረጀ እና መታገስ ዓለሜ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ የወንጀል ችሎት መቅረባቸው ይታወሳል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይም የሽብር ወንጀል ስልጣንን በኃይል ለመያዝ፣ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በመደራጀት፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ቡድን አመራሮች ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ መንግሥት የሕዝብ ተቀባይነት እንዲያጣና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ እንዲደረግበት በማሰብ፣ ተዋድደውና ተከባብረው በሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠርና ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ፣ በውጭ ሀገር ከሚገኝ የፀረ ሰላም የቡድን አመራሮች ጋር በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት እና ተልዕኮ በመቀበል የሥራ ባህሪያቸውን እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም የሚሉ የምርመራ የጥርጣሬ መነሻዎች ለችሎቱ ቀርበዋል፡፡

ፖሊስ ባለፈው ቀጠሮ በተሰጠው 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያከናውናቸውን ተግባራት ዛሬ ለፍርድ ቤቱ በዝርዝር አቅርቧል።

በዚህም መሠረት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከተቋማት የተለያዩ መረጃዎችን መሰብሰብ እና ምስክሮችን የመስማት ሥራ ማከናወኑን ለችሎቱ አብራርቷል።

የምርመራ ሥራውን በሰውና በሠነድ ማስረጃ በስፋት ለማጣራት፣ ቀሪ የፎረንሲክ እና የቴክኒክ ምርመራዎችን ለማጠናቀቅ እንዲቻል 14 ተጨማሪ ቀናት ይፈቀድልኝ ሲልም ፍርድ ቤቱን ዛሬ ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቃዎች በበኩላቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ ቋሚ አድራሻ ያላቸው እና መረጃም የማያጠፉ መሆናቸውን ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው ሊከበር ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ፖሊስም ተጠርጣሪቹ የዋስትና መብት ቢፈቀድላቸው መረጃ ሊሰውሩ እንደሚችሉ እና ምስክሮችንም በጥቅም በመደለል ሊያሸሹብኝ ይችላሉ ሲል ተቃውሟል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎትም፤ ፖሊስ ቀሪ ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ ተጨማሪ 12 የምርመራ ቀናት ፈቅዷል፡፡

በሲፈን መኮንን

Exit mobile version