Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ብቁ አመራር በመፍጠር ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ በአፍሪካ ብቁ የመከላከያ አመራር በመፍጠር ረገድ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተገለጸ።

በሜጀር ጄኔራል ዳሂሩ ሳኑሲ የተመራ የናይጄሪያ ወታደራዊ ልዑካን ቡድን የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅን እንዲሁም የመከላከያ ሠላም ማሥከበር ማዕከልን ጎብኝቷል።

የቡድኑ መሪ ሜ/ጄኔራል ዳሂሩ ሳኑሲ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ መረጋጋት ጠንካራ የፀጥታ ተቋማትን በመፍጠር ረገድ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የናይጄሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ረጅም አመታትን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው፤ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለአፍሪካ ሀገሮች ብቁ አመራር በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

የልዑካን ቡድኑ በመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከልን ሲጎበኝ ገለጻ ያደረጉት የማዕከሉ ዘመቻ ክትትልና ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል መኮንን አስፋው፤ ኢትዮጵያ የሠላም ማስከበር ተልዕኮን በስልጠና እና በስትራቴጂ በመከወን ሽብርተኝነትን እና ፅንፈኝነትን በመከላከል ከፍተኛ ሚና እየተወጣች ትገኛለች ብለዋል።

ጉብኝቱ ትብብርን የሚያጠናክር ወታደራዊ ዕውቀትና ልምድ ለመለዋወጥ እና በጋራ ለመስራት በር የሚከፍት መሆኑን መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version