የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመከላከያ ልዕልና እና የላቀ ብቃት ማሳያ ነው – አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)

By Mikias Ayele

April 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመከላከያ ልዕልና እና የላቀ ብቃት ማሳያ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ገለፁ፡፡

ሚኒስትሯ በኢፌዴሪ አየር ኃይል የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን÷በዚህ ወቅትም ተቋሙ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አድንቀዋል።

አየር ኃይሉ ብቃቱን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ ዕድገትና ሀገራዊ ግዴታን በመወጣት ረገድ እያሳየ ያለው ብቃት በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በተለይም የጥገና ወጪን በራስ አቅም ለመሸፈን ያከናወናቸው ተግባራት የሀገርን ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ ለማዳን ማስቻሉን አመልክተዋል።

የተቋሙን መሰረተ ልማቶች በማዘመንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።

የተቋሙን ዝግጁነትና ስትራቴጂካዊያዊ ዕድገት የበለጠ ለማረጋገጥና ለማፅናትም ሚኒስቴሩ ድጋፉን እንደሚጠናክር ቃል ገብተዋል።

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው÷አየር ኃይሉ በሰው ኃይል፣ በጥገናና በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ የደረሰበትን ደረጃ በማስመልከት ገለጻ ማድረጋቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።