አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ጎልጋ እንደገለፁት÷በክልሉ በክህሎት የሚመራና ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ባለፉት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሥራ ፈላጊዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ለ244 ሺህ አዳዲስና ነባር ሰልጣኞች ብቃትና ጥራት ያለው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በአጫጭር ስልጠና ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሥራ ፈላጊዎችን በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት፣ 5 ሺህ 702 ሼዶች እና ከ5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለኢንተርፕራይዞች እንደተሰራጨ መጠቆማቸውንም የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡