Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዓመታዊ ገቢ 48 ቢሊየን ብር ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተተገበሩ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ (ኢባትሎ) ዓመታዊ ገቢ ከነበረበት 17 ቢሊየን ብር ወደ 48 ቢሊየን ብር ማደጉ ተገለጸ።

የኢባትሎ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ዘርፉ በቂ የፖሊሲ ድጋፍ ያልነበረውና ችግር ውስጥ የቆየ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የኢባትሎን አሰራር ይበልጥ ሊያቀላጥፉ የሚችሉ ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ለተመዘገበው ውጤት ሚና እንደነበራቸው ጠቁመዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች የብሔራዊ ሎጂስቲክስ ካውንስል መቋቋሙን ጠቁመው፤ የኢባትሎን አሰራር ይበልጥ ሊያቀላጥፉ የሚችሉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች መተግበራቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ የተደረጉት የለውጥ ሥራዎች ተቋሙ ከኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ እንዲሆን ማስቻላቸውን አብራርተዋል።

ኢባትሎ በ350 ወደቦች የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ዓመታዊ ገቢው ከ17 ቢሊየን ብር ወደ 48 ቢሊየን ብር ማደጉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ለግል ኦፕሬተሮች የሚሰጥ ፈቃድ ተወዳዳሪና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

Exit mobile version