አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ችግሮችን ለመፍታት አውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ቀጣናዊ ችግሮችን ለመፍታት አካታች የሆነ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሁም የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ አውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
አኔት ዌበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተጫወተች ያለውን አዎንታዊ ሚና አድንቀው፤ በቀጣይ የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ቁጠኝነት ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።