Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገራዊ ልማት የሁሉንም ርብርብ ስለሚጠይቅ ሕዝቡን አስገንዝቦ ማነሣሣት ላይ ሊተኮር ይገባል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሀገራዊ ትልሞችንና የመዳረሻ ግቦችን ማስገንዘብ ላይ በትኩረት መስራት እንደለበት የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ለክልል እና ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቅቋል።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሠረተ ሐሳቦችንና የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህም የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሀገር ልማት የሁሉንም ርብርብ ስለሚጠይቅ ምልዓተ ሕዝቡን አስገንዝቦ ለላቀ ተሳትፎ እና ስኬት ማነሳሳት ላይ አተኩሮ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ይዘቶቹ የኢትዮጵያን ተስፋዎች፣ የዕድገት መሠረቶች፣ የልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ፋይዳ፣ ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ ማመላከት ላይ አተኩረው መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

አክለውም ከተያዘው በጀት ዓመት መግቢያ ጀምሮ ወደ ተሟላ የትግበራ ምዕራፍ የገባው 2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ስኬቶች እንደተመዘገቡበት ተናግረዋል።

ለአብነትም ባለፉት 9 ወራት ከወጪ ንግድ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው÷ካለፈዉ በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም አንጻር የ150 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አጠቃላይ የመንግሥት ገቢም ከ926 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን ገልጸው÷ ካለፈዉ በጀት ዓመት አንጻር የ135 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ነው ያስረዱት፡፡

ኢትዮጵያ በ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተረጋጋ ማክሮ-ኢኮኖሚ እና ምቹ የኢንቨስትመንት እና የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዘርፎችን ምርታማነትና ውጤታማነት ለማሳደግ እና ብቃት ያለው ውጤታማ የሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው ማለታቸውንም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version