የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ኦርዲን በድሪ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

By Yonas Getnet

April 12, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ዜጎች በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መስጫ ማዕከላት በመገኘት እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የምዝገባ ሒደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አቶ ኦርዲን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፋይዳ ታማኝነትን የሚዘረጋ፣ የተቋማትን ስራ የሚያቀናጅ፣ በግለሰቦች ደረጃም የራስን መብት የሚያስጠብቅ ነው።

የሀገርን እና የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ማስገንዘባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም እንደ ሀገር ለተጀመረው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በየማዕከላቱ የብሔራዊ መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችል ምዝገባ በልዩ ትኩረት በመተግባር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መያዝ እንደሀገር አስገዳጅ መሆኑን በመረዳት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በአካባቢው በሚገኙ የምዝገባ ማዕከላት በመሄድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።