አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢ-መደበኛ ጦርነት እና ጸረ-ሽምቅ ውጊያን ለማከናወን ስትራቴጂያዊ እና አውዱን የሚረዳ አመራር መገንባት
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢ-መደበኛ ጦርነት እና ጸረ-ሽምቅ ውጊያን ለማከናወን ስትራቴጂያዊ እና አውዱን የሚረዳ አመራር መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌ/ጄ ሹማ አብደታ አስገነዘቡ፡፡
ሌ/ጄ ሹማ አብደታ በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ለ3ኛ ዙር መደበኛ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት ጄኔራል መኮንኑ እንዳሉት÷ኢ-መደበኛ ጦርነት እና ጸረ-ሽምቅ ውጊያን ለማካሄድ አውዱን የተረዳ እንዲሁም መቼና የት ሊከሰት ይችላል የሚል ስትራቴጂያዊ አመራር መገንባት ይገባል ብለዋል፡፡
እነዚህን ነጥቦች በጥንቃቄ ማከናውን ከተቻለም የሚከሰተን ኢ-መደበኛ ጦርነት እና ጸረ-ሽምቅ ውጊያ በበላይነት ማጠናቀቅ ይቻላል ነው ያሉት፡፡
በትንሽ ኪሳራ ትልቅ ድል ማስመዝገብ የሚቻልው አመራሩ ራሱን በማብቃት ፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንባት ሲችል እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም መከላከያ እንደ ተቋም በርካታ ሥራዎችን እያከነወነ እንደሚገኝ መናገራቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ተማሪዎች የሚማሩት የወታደራዊ ሳይንስ ንድፈ-ሃሳብ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚዛመድ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡