Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ባለፉት 9 ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ስኬታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ስኬታማ አፈጻጸም መመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉት 9 ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።

በመድረኩ የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በአራቱም ምሶሶዎች የተሻለ ስኬት መመዝገቡን አብራርተዋል፡፡

ይህም የ8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስዝገብ የተያዘውን እቅድ እንደሚሳካ ያመላከተ ነው ብለዋል።

የ2ኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የዘርፎች ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት ንግድን ከባቢማሳደግ እንዲሁም የመንግስት የመፈጸም አቅምን ማጎልበትን ዓላማ አድርጎ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ኢንቨስትመንትና ቁጠባ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ያላቸው ድርሻ መሻሻሉንና ከሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት አኳያ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 20 ነጥብ 5 ወደ 23 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን አንስተዋል።

የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ላይ የተሻለ አፈጻጻም ማስመዝገቡን እና የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢኮኖሚ እድገትን ከማሳለጥ ባሻገር 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የእዳ ሽግሽግ ማምጣቱን ተናግረዋል።

በእዳ ውስጥ የነበሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በሪፎርም ስራው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥራ ወደ ትርፋማነት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት 9 ወራት መንግስት ምንም ዓይነት ብድር ከብሔራዊ ባንክ አለመውሰዱን ጠቅሰው÷ ይህም የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ትልቅ ፋይዳ ማበርከቱን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል መንግስት የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ ጫና እንዳያሳድር ለሴፍትኔት፣ ለመሰረታዊ ፍጆታ፣ ለነዳጅና ሌሎች ስትራቴጂክ ምርቶች የሚያደርገውን ድጎማ አጠናክሮ እንደቀጠለ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሀገር ውስጥ፣ በውጭ እና በርቀት የሥራ እድል ፈጠራ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ሚኒስትሯ በሪፖርቱ አመልክተዋል፡፡

Exit mobile version