አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ከ29 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለመትከል መዘጋጀቱን የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መስፍን ቃሬ ከ32 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ከ29 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል፡፡
በ4 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ አዲስ ቡናን ለመትከል ከጥር ወር ጀምሮ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መቆፈራቸውንና በያዝነው ወር ተከላው እንደሚጀመር አስረድተዋል፡፡
የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቡና ተክል አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ እንዲሁም ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን ነቅሎ በአዲስ የመተካት ስራ እየተሰራ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጉንደላና ነቅሎ በመተካት ሥራ ባለፈው ዓመት 8 ሺህ ሄክታር ማሳ ማደስ እንደተቻለ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ÷ በዚህ ዓመት 11 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ ላይ የሚገኝ ቡና መታደሱን ገልጸዋል፡፡