አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት 9 ወራት 98 ሺህ ቶን የሚጠጋ የድንጋይ ከሰል ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገበረማርያም ሰጠኝ እንደገለጹት÷ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል የድንጋይ ከሰል አንዱ ሲሆን፤ በክልሉም በሰፊው ይገኛል።
ቀደም ሲል ሃብቱ ተገቢው ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ለአካባቢው እና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዳላበረከተ አስታውሰዋል።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከዘርፉ የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት በተወሰዱ ርምጃዎችና ወደምርት ሥራ በመገባቱ የድንጋይ ከሰሉን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት 200 ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማዕከላዊ ከበያ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት 9 ወራት 98 ሺህ ቶን የሚጠጋ የድንጋይ ከሰል ማቅረብ ተችሏል ብልዋል።
በዘርፉ ለመሰማራት ፍቃድ ከወሰዱ ከ20 በላይ ማህበራት መካከል በአሁኑ ወቅት ወደምርት የገቡት ስምንት ብቻ መሆናቸውንም ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡