አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ም/ቤት 26ኛ መደበኛ ስብሰባ በቀረቡለት አጀንዳዎች ላይ በመምከር ማምሻውን ተጠናቋል።
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ÷ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ሁሉንም የምርት ወቅቶች ታሳቢ ያደረገ ልማት ማከናወን መቻሉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ተጨማሪ ወቅቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አንስተዋል።
በክልሉ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው ÷ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ በ35 ወረዳዎች ልዩ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ምርት ወደ ገበያ እንዲቀርብ እና ለኤክስፖርት ድርሻ እንዲኖረው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ነው ያብራሩት፡፡
የምርት አቅርቦቱን ይበልጥ በማጠናከር ከሰንበት እስከ ሰንበት የተጀመሩ የግብይት ሥፍራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዜጎችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን እንዲሁም የወጣቶችን እና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።
ከተሞችን ለማዘመን፣ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር እና መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት አገልግሎት አሰጣጡ ወደ ዲጂታል ሥርዓት እየተቀየረ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት 9 ወራት በአጠቃላይ በኮሪደር ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በበከተማ ልማት፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና እንዲሁም በገቢ አሰባሰብ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ማለታቸው የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡