አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የጨቅላ ህጻናትና እናቶች ሞት ምጣኔን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀናትና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ግምገማ መካሄዱ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ አበይት ተግባራት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የተያዙ ዕቅዶች በአግባቡ መከናወናቸውን ገልጸው÷ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞትን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ጤና ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻልና መሰረተ ልማትን በማሟላት የመጣ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ደግሞ ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በተሰጠው ትኩረት ህብረተሰቡ አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኙ ያስቻለ ነው ብለዋል።
የባለሙያ፣ የጤና ተቋማት እና ግብዓት አቅርቦትን አንድ ላይ ለማስተሳሰር የተሰራው ስራ የእናቶችና ህጻናት ሞት ምጣኔ የቀነሰ ከመሆኑም ባሻገር የህብረተሰቡ ጤና የጠበቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የማህበረሰብ ጤና መድህን አገለግሎትን በማስፋፋትም ውጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉን አክለዋል፡፡
የጤና ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ስራም ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰው÷ በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለማቃለል በተሰሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለዩ 19 ማዕከላት ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ መደረጋቸውን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
ዳያስፖራውን ጨምሮ ህብረተሰቡን በማስተባበር በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ፣ ወሊድ አገልግሎትና ቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች መሰጠታቸውን አብራርተዋል፡፡
የአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ትኩረት ካደረጋቸው ተቋማት ውስጥ ጤና ተቋሙ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው÷በቀሪ ወራት ያልተጠናቀቁ ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡