አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእግር ኳሱ ዓለም እያስመዘገበ ያለውን ስኬት ተከትሎ ከትውልድ ሀገሩ አልፎ አፍሪካን እያስጠራ ያለውን የወቅቱ ስመ ጥር የእግር ኳስ ጠቢብ ሞሐመድ ሳላህ በወፍ በረር እናስቃኝዎ፡፡
በሀገረ ግብጽ የምትገኘውን የትውልድ መንደሩን ተላብሷት “የናግሪግ ልጅ” እየተባለ መጠሪያ እስከማድረግ የደረሰው፤ ሞሐመድ ሳላህ ከወንድሙ ናስር ሳላህ እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ጋር ሆኖ ዕድገቱን በመንደሩ አሳልፏል፡፡
በሰባት ዓመቱም ከወንድሙ ጋር በመሆን በናግሪግ እግር ኳስ መጫወት መጀመሩን ያስታውሳል፡፡
ቀን ከእኩዮቹ ጋር ኳስ ሲጫዎት ይውላል፤ ምሽት ላይ ደግሞ አርዓያዎቹ እንደሆኑ የሚያነሳቸውን ሮናልዶ ናዛሪዮ፣ ዚነዲን ዚዳን እና ቶቲን በቻምፒየንስ ሊጉ በመመልከት የልጅነት ጊዜውን ማሳለፉን ይናገራል፡፡
የእግር ኳስ ፍቅር የብዙ ቤተሰቦቹ አባላት እንደሆነ የሚገልጸው ሞሐመድ ሳላህ፤ ለአብነትም አባቱ ሳላህ ጋህሊ እና ሁለት አጎቶቻቸው ከኳስ ወዳድነት አልፈው የናግሪግ ወጣት ቡድንን በተጫዋችነት ማገልገል ችለዋል፡፡
ሞሐመድ ሳላህም እንደ ቤተሰቡ ሁሉ በልጅነቱ በኤልሞካውሎን ፕሮፌሽናል እግርኳስን በ14 ዓመቱ እንደጀመረ ግለታሪኩ ያስረዳል፡፡
የኤልሞካውሎን የወቅቱ አሰልጣኝም “ሳላህ ለተከላካዮች ፈታኝ ተጫዋች ነው” ሲሉ አሞካሽተውታል፤ ከዚህ ምስክርነት በላይ የሆነ ስኬታማ ጊዜ በክለቡ ካሳለፈ በኋላም ወደ ባዜል ማቅናት ችሏል፡፡
በባዜል ባሳየው ብቃትም የእንግሊዙን ክለብ ቼልሲ ትኩረት መሳቡን ተከትሎ፤ በፈረንጆቹ 2014 ወደ ለንደኑ ክለብ ማቅናቱ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ በቼልሲ ቤት ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ያልቻለው ሞሐመድ ሳላህ፤ በውሰት ወደ ፊዮረንቲና ከፊዮረንቲናም ወደ ሮማ ለማቅናት ተገድዷል፡፡
በሮማም ስኬታማ ጊዜ አሳለፈ፤ ክለቡ ሳላህን ባስፈረመበት ዓመት በሴሪ ኤው 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ቻለ፡፡
በዚህ የሮማ ስኬታማ ደረጃም የሞሐመድ ሳላህ ሚና የጎላ እንደነበር ይነሳል፡፡ ለአብነትም የሮማ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን መቀዳጀት መቻሉ ይጠቀሳል፡፡
በሮማ የሁለተኛ ዓመት ቆይታው ወቅት በነበረው ድንቅ አቋም የተማረከው የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል በፈረንጆቹ 2017 ሞሐመድ ሳላህን አስፈርሞ የግሉ አደረገ፡፡
ሳላህ ወደ ሊቨርፑል በመጣበት ዓመትም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሽልማትን ያሸነፈ ሲሆን፤ በተጨማሪም በዚሁ ዓመት የፕሪምየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች መባል ችሏል።
ሊቨርፑል ባስፈረመው ዓመት የክለቡ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት እና የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፏል፡፡
ሞሐመድ ሳላህ ብቃቱን ተከትሎ በሊቨርፑል ዝነኛ ተጫዋች መሆን ቻለ፤ ከዝናው ባሻገር በአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ እየተመራ ከሳዲዮ ማኔ እና ፈርሚኖ ጋር አስደናቂ ጥምረትን በመፍጠር ቀዮቹን ወደ ታላቅነታቸው መመለስ ቻለ።
በዚህም ሊቨርፑል ለ30 ዓመታት ርቆት የነበረውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሳካ፤ በተጨማሪም የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ከፍ ማድረግ ቻለ፡፡
በክሎፕ የአስልጣኝነት ዘመን ሊቨርፑልን የትኛውም ክለብ ሊገጥመው የሚፈራው ቡድን እንዲሆን ትልቁን ሚና ከተወጡ የቡድኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሞሐመድ ሳላህ ሆነ።
አሁን ላይ ሊቨርፑል 20ኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሞሐመድ ሳላህ ትልቁን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።
በዚህ የውድድር ዓመት የሊጉ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ ከጫፍ የደረሰው ሳላህ፤ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በርካታ ክብረወሰኖችን እየተጋራ ይገኛል፡፡
ከሊቨርፑል ጋር ለሁለት ዓመታት የሚያቆውን ውል ባደሰበት ሣምንት፤ በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ የጎል አስተዋፅኦ በማድረግ ከአለን ሺረር እና ከአንድሪው ኮል በመቀጠል ሦስተኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡
በቀሪ ጨዋታዎች ጎል የሚያስቆጥር ወይም ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ የሚያቀብል ከሆነ አለን ሽረርን እና ኮልን በመብለጥ ክብረወሰኑን በእጁ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ትጋቱን እንደሚያስቀጥል ይጠበቃል፡፡
ከእግር ኳስ ውጭም የተረጋጋ ኑሮ እንዳለው የሚገለጽለት ሳላህ፤ ገና በትምህርት ቤት ሳለ ከተዋወቃት ማጊ ሳዲቅ ጋር በፈረንጆቹ 2013 ትዳር መስርተው፤ በ2014 ማካ እና በ2020 ካያን የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
ከእግር ኳስ ውጭ ያለውን ጊዜም፤ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን፣ ፊልም በማየት፣ ቴብል ቴኒስ በመጫወት፣ ቪዲዮ ጌሞችን በመጫወት እና ዋና በመዋኘት እንደሚያሳልፍ የሕይዎት ታሪኩ ያስረዳል፡፡
ሞሐመድ ሳላህ ወደ ቼልሲ ከማቅናቱ ከጥቂት ሣምንታት በፊት በግብፅ ሕገ-መንግሥት መሠረት፤ ከውትድርና ግዳጅ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር።
በሀገሩ ሕግ መሠረት የመጀመሪያ ዲግሪውን ያልያዘ (ያልጨረሰ) ወንድ የውትድርና ትምህርት የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሞሐመድ ሳላህ የግዳጅ ጥሪ የቀረበበት ሲሆን፤ የትምህርት ሂደቱን መረጃ ማስገባት በሚጠበቅበት ጊዜ ሳያስገባ እንደቀረ ይነሳል፡፡
በወቅቱም የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃ፤ ሞሐመድ ሳላህ ወደ ግብፅ ከተመለሰ ከ1 እስከ 3 ዓመታት ድረስ ከግብፅ እንዳይወጣ ሊታገድ እንደሚችል መዘገባቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ ሳላህ በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር በመነጋገር ችግሩን ፈታ፤ ይህም ወደ ግብፅ ሲመለስ ከሀገሩ ከ1 እስከ 3 ዓመታት እንዳይወጣ የሚያደርገውን ሕግ አስቀረለት፡፡
የግብፅ ብሔራዊ ቡድን የወቅቱ ዳይሬክተር የነበሩት አሕመድ ሃሰን፤ ሳላህ ለሀገሩ በእግር ኳሱ እያደረገ ያለውን እና ሊያደርግ የሚችለውን በመግለፅ “ሀገርን ከዚህ በላይ ማገልገል አይጠበቅበትም” ሲሉ ዘብ ቆመውለታል፡፡
አሕመድ ሃሰን ስለ ሞሐመድ ሳላህ ያደረጉት ይህን ድንቅ ንግግርም ልክ መሆኑን ከ10 ዓመታት በኋላ ዓለም ተመልክቷል፡፡
ሳላህ ምንም እንኳን ለሀገሩ የአፍሪካ ዋንጫ ባያመጣም፤ በፈረንጆቹ 2017 እና በ2021 ግብጽን ለፍፃሜ አብቅቷል፡፡
ለፍጻሜ እየደረሱ ዋንጫ ቢያጡም ግብፅ ስትነሳ ሞሐመድ ሳላህ፤ ሞሐመድ ሳላህ ሲነሳ ግብጽ መነሳታቸው አይቀሬ እንዲሆን ማድረግ ችሏል።
በብሔራዊ ቡድን ቆይታው ለሀገሩ ዋንጫ ባያመጣም፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ከስሙ ጋር ሀገሩን ከፍ እያደረገ ነው፡፡
ከሀገሩ ግብፅ አልፎም በየሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ሁሉ በየትልልቅ ግጥሚያዎች ጭምር አፍሪካን ያስጠራል፡፡
ሞሐመድ ሳላህ ከትንሿ ናግሪግ መንደር እስከ ስዊዘርላንድ ባዜል – ከባዜል እስከ እንግሊዝ – ከእንግሊዝ መርሲሳይድ እስከ መላው ዓለም ስሙን በወርቅ ቀለም ያጸፈ የወቅቱ ስመጥር አፍሪካዊ የእግር ኳስ ጠቢብ ሆኗል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ