አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሣምንት ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሣምንት) ይባላል፡፡
ዛሬ የሰሙነ ሕማማት ሣምንት ሁለተኛው ቀን ነው፡፡
ይህ ሣምንትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ እንደየሃይማኖቱ አስተምኅሮዎች በመጾም፣ በመስገድ እና ጸሎት በማድረግ ያልፋል፡፡
“ሰሙን” ሳምንት ማለት ሲሆን፤ ሕማማት ደግሞ “ሐመ” ታመመ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ እና መታመም፤ መሠቃየት የሚል ፍቺ ያለው ቃል ነው፡፡
የሁለቱ ቃላት ጥምረትም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕመሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሣምንት መሆኑን ይገልጻል ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል መምህራን ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል ሰሙነ ሕማማት የኦሪት ዘመን ምሳሌ ስለመሆኑም ይገልጻሉ መምህራኑ፡፡
በዘመነ ኦሪት (አዳም ከገነት ከተባረረበት ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም እስከተወለደበት ዘመን) የሰው ልጅ የጽድቅ ሥራው ለመንግሥተ ሰማያት የማያበቃው እንደነበርም ያወሳሉ፡፡
ይልቁንም ነቢዩ “ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ’’ (ኢሳ 64:6) እንዳለ፤ የአዳም ዘር በሙሉ እስከ ዕለተ ዐርብ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ የሰው ልጅን እስካዳነበት ድረስ የሰው ልጆች በዲያብሎስ በባርነት ሥር ነበሩና ሰሙነ ሕማማትም የዘመነ ፍዳ ምሳሌ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸክሞአል” (ኢሳ.53:4) እንዳለ፤ በክርስቶስ ክቡር ደም የዳነ ክርስቲያን መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ሞት ስለ እኔ ኃጢአት ነው ብሎ በማመን በጸሎት፣ በጾምና በስግደት ሆኖ ክብርን ሁሉ ለአምላኩ የሚሰጥበት ወቅት እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
በዚህ መሠረትም ሰሙነ ሕማማት ለአማኞች የቅድስና እና የመንፈሳዊ ሀብት መገኛ ወቅት ነው ይላሉ፡፡
በዮሐንስ ደርበው