አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በዋናው ቄራ እና አቃቂ ቅርንጫፍ ቄራ 6 ሺህ 500 እንስሣት ለዕርድ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀ።
ለዕርድ እንደሚቀርቡ ከሚጠበቁት እንስሣት መካከልም 4 ሺህ በሬዎች እንዲሁም 2 ሺህ 500 ያህሉ በግ እና ፍየል እንደሚሆኑ የድርጅቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አታክልቲ ገ/ሚካኤል ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ስኬታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ዘርፈ-ብዙ ዝግጅት ማድረጉንም አረጋግጠዋል፡፡
ለአብነትም ተቋሙ ካሉት 1 ሺህ 41 መደበኛ ሠራተኞች ባለፈ 260 ተጨማሪ ጊዜያዊ ሠራተኞች ቅጥር ማከናወኑን እና አስፈላጊውን ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
የእርድ ክፍሎች አጠቃላይ እድሳት መደረጉን ጠቁመው፤ አጠቃላይ የእርድ ማሽኖች ጥገናና እድሳት መከናወኑንም አስረድተዋል፡፡
ከ40 በላይ የሥጋ መኪናዎች ዝግጁ ናቸው ያሉት አቶ አታክልቲ፤ ሌሎች በርከት ያሉ ድጋፍ ሰጭ ተሽከርካሪዎችም ጥገናና እድሳት እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡
በተረፈ-ምርት የሚገኙ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች ሁሉም ተጠግነውና ታድሰው ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከ60 ሚሊየን ብር በላይ የተገዛ ተረፈ ሥጋን የሚያቀነባብር ማሽን ተገዝቶ መተከሉን አንስተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው