አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በይፋዊ ጉብኝታችን ወቅት ላደረጉልን የደመቀ አቀባበል እና የክብር መስተንግዶ አመሰግናለሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያና ቬትናም የሚያመሳስሏቸው ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሏቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ሁለቱም ሀገራት ትልቅ እና ለሥራ የተነሳሳ ወጣት ሕዝብ ያላቸው፣ ለልማት እና እድገት የቆረጡ እንዲሁም በታሪካቸው ሂደትም በፅናታቸው የሚታወቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በንቁ ተሳትፎ የሚገለጥ እና ጥልቀት ያለው ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው÷ ለጋራ እድገት እና ትብብር ያለው ፅኑ የጋራ ተነሳሽነት መንጸባረቁንም አመላክተዋል።
የሃሳብ ልውውጣችን በሁለቱ ሀገራት መካከል ለጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በር ከፍቷል ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቅርብ ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት የጋራ ርዕዮቻችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እና በዛሬው የዓለማችን አውድ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ይበልጥ የምናፀናበት ይሆናል ሲሉም ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።