Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በድሬዳዋ ባለፉት 9 ወራት በልማት እና መልካም አስተዳደር ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ የሴክተሮችና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ዛሬ ተገምግሟል።

ግምገማውን የመሩት ከንቲባው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአስተዳደሩ በከተማና ገጠር ክላስተር በተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በመስኖ ልማትና በሌማት ትሩፋት የተተገበሩ ውጥኖች ማህበረሰቡን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

ድሬዳዋን ምቹና ማራኪ የስራ እና የመኖሪያ ከተማ ለማድረግ የተጀመረው የ11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት 86 በመቶ መጠናቀቁንም አንስተዋል።

በተጨማሪም በየተቋማቱ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ዘመኑን የሚመጥን ምቹ አደረጃጀቶችን በመዘርጋት ለተገልጋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣዮቹ ወራትም እነዚህን ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተቋማት እና አመራሮች በተገኘው ውጤት ሳይዘናጉ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

Exit mobile version