አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውል የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳለ በጥናት መረጋገጡን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ኢንስቲትዩቱ የሀገር ውስጥ የምርምር አቅም እንዲጠናከር በማድረግ በተለያዩ የሥነ-ምድር ጥናት ዘዴዎች ምርምር እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
በተለያዩ አካባቢዎች የማዕድን ሃብት ፍለጋ ጥናት እና ምርምር የሚያደርገው ኢንስቲትዩቱ፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ውስጥ ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረጉን ገልጿል።
በዚህም የተገኘውን የድንጋይ ከሰል ክምችት ናሙናዎች በኢንስቲትዩቱ የጂኦሳይንስ ምርምር ላቦራቶሪ ማዕከል ተፈትሸው ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚያገለግል መሆኑን መረጋገጡን አመልክቷል።
በዘርፉ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው አልሚዎች ከተቋሙ የጂኦሳይንስ መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ አስታውቋል።