Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኮርፖሬሽኑ የ3ዲ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ወደ ኢትዮጵያ ሊያስገባ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የ3ዲ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ለማስገባት ከኦስትሪያው ግዙፍ የግንባታ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ባውሚት ግሩፕ ጋር ተስማምቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል÷ከኩባንያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የ3ዲ የኮንስትራክሽን ፕሪንትን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በኦስትሪያ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ረሻድ÷ተጨማሪ ተሞክሮ ለመቀመር በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተሰናዳው የኮንስትራክሽን ማሽንና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይም ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በፊት የአልሙኒየም ፎርም ወርክ የግንባታ ቴክኖሎጂን ከኦቪድ ጋር በመሆን ከደቡብ ኮሪያ በማስመጣት በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የፕሪካስት የግንባታ ቴክኖሎጂን ከዋንኮ ኢታሊ ኩባንያ ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡

የአሀኑን ስምምነት ተከትሎ የ3ዲ ኮንስትራክሽን ፕሪንት የግንባታ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያስተዋወቀው 3ኛው ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ለመሆን ያስችለዋል ተብሏል፡፡

ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ፍላጎትና በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየውን የግንባታ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው መጠቆሙን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የ3ዲ የኮንስትራክሽን ፕሪንት ከተለመደው የግንባታ ዘዴ ጋር ሲነጻጸር የግንባታ ወጪን ከግማሽ በላይ የሚቀንስና ውስብስብ አርክቴክቸራል የቤት ዲዛይኖችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ተጠቅሷል፡፡

ቴክኖሎጂው 98 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ የሚጠቀም ሲሆን÷ግዙፍ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችንና የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን በወራት እድሜ ለማጠናቀቅ ያስችላል ተብሏል፡፡

Exit mobile version