የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ990 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

By Melaku Gedif

April 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለ990 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዳሉት÷ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር ያሳዩና በሕግ በተደነገገው አግባብ የይቅርታ መስፈርትን ያሟሉ ናቸው፡፡

ይቅርታ ከተደረገላቸው 990 የሕግ ታራሚዎች መካከል 985ቱ በሙሉ ይቅርታ ከእስር የሚፈቱ ሲሆን÷ ቀሪ 5 ታራሚዎች ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የሕግ ታራሚዎች መካከል 73ቱ ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ 917ቱ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ታራሚዎቹ የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን የበደሉትን ህብረተሰብ በማገልግል በልማት ሊክሱ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡