አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓልን ተገን አድርገው ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸው ምግቦች ወደ ማሕበረሰቡ እንዳይደርሱ እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ፡፡
በቅቤ፣ ማር፣ በርበሬ እና እንጀራ ላይ ባዕድ ነገሮች ቀላቅለው ለገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች እንዳሉ የጠቆሙት የባለስልጣኑ የቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንጋ እርቀታ፤ ክትትል በማድረግ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ወደ ገበያ የሚገቡ ምግቦች የሚመጡበትን ሂደት ጨምሮ በአግባቡ ስለመያዛቸው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ባለስልጣኑ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት በራሱ መዋቅር ከሚያደርገው ክትትል በተጨማሪ የማሕበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ባለስልጣኑ እንደሚረዳ ጠቁመው፤ ለዚህም በየክፍለ ከተማው የማሕበረብ የቁጥጥር ፎረም መቋቋሙን ጠቅሰዋል፡፡
አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲኖሩም ሕብረተሰቡ በ8864 ነጻ የስልክ መስመር ደውሎ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በብርሃኑ አበራ