ስፓርት

ሙሉጌታ ምህረት …

By Hailemaryam Tegegn

April 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዳነ ግርማ እና ሽመልስ በቀለን የመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ካበረከተው የሀዋሳ ኮረም ሜዳ ነው የእግር ኳስ ህይወቱ የጀመረው።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ሶስት ጊዜ ማሳካት የቻለው ሙሉጌታ ምህረት ከኳስ ብቃቱ ባልተናነሰ በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ የሚወሳ መልካም ምግባር ባለቤት ነው፡፡

በ16 አመታት የክለብና የብሔራዊ ቡድን የተጫዋችነት ቆይታው አንድም ቀይ ካርድ አለመመልከቱና በእነዚያ ሁሉ አመታት አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ ማየቱ የዚህ ማሳያ ነው፡፡

የሙሉጌታ ምህረት ስኬታማ የተጫዋችነት ጉዞ የጀመረው በሀዋሳ ኮረም ሜዳ ነው፡፡ ኮረም ሜዳ ከ31 አመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በተመለሰው ታሪካዊው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ተጫዋቾች መካከል ሽመልስ በቀለ እና አዳነ ግርማን ያስገኘች ሜዳ ናት፡፡

በዚህች ሜዳ አልፎ ሀዋሳ ከነማን በአምበልነት እየመራ የፕሪሚየር ሊጉንና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ያሳካው ሙሉጌታ፤ በተወዳጁ የወቅቱ የሀዋሳ ከነማ አሰልጣኝ ከማል አህመድ ዐይን የገባው በሀዋሳ ሲካሄድ በነበረ የፋብሪካዎች የእግር ኳስ ውድድር ወቅት ነበር፡፡

ሙሉጌታ ምህረት በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ ሲናገር በወቅቱ በተክለ ሰውነቱ ቀጭን ስለነበረ አሰልጣኝ ከማልን ጨምሮ ብዙዎች የኳስ ብቃቱን ተጠራጥረው እንደነበር ገልጿል፡፡

ሀዋሳ ከነማ በ1996 የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚው የክልል ክለብ መሆን የቻለበትን ደማቅ ታሪክ ሲጽፍ፥ ሙሉጌታ ምህረት ደግሞ የአመቱ ኮከብ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፏል፡፡

በቀጣዩ አመትም ክለቡ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት ሲሆን፥ የአምበሉ ሙሉጌታ ምህረት ሚና ላቅ ያለ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚያም በ1998 ወደ ጊዮርጊስ በማቅናት ከክለቡ ጋር የፕሪሚየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አሳክቷል፡፡

ከዚያም ዳግም ወደ ሀዋሳ ከነማ በመመለስ በ1999 ክለቡ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያሸንፍ ሙሉጌታ የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመሆን በድጋሚ ተሸልሟል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያሳካውን የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሴካፋ ዋንጫን ጨምሮ ከሀዋሳ ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት ጋር በመሆን በርካታ ዋንጫዎችን አንስቷል።

ሙሉጌታ ምህረት በ16 አመታት የተጫዋችነት ቆይታው ተደጋግመው ከሚነገሩ ጉዳዮች አንዱ በእነዚያ ሁሉ አመታት አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ መመልከቱ እንዲሁም አንድም ጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት አጋጣሚ አለመኖሩ ነው፡፡

ቀይ ካርድ አለመመልከቱ ራሱም ጭምር የሚገረምበት ሁኔታ መሆኑን የሚገልጸው ሙሉጌታ፤ ጠንከር ያለ አጨዋወትን የሚከተል ተጫዋች እንደነበር ይናገራል።

ምናልባትም ለካርድ እንዳይጋለጥ ያደረገው ሁሌም በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚፈጸሙ ጥፋቶች ይቅርታ የመጠየቅ ልምዱ ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻል።

የሙሉጌታ ምህረት የተጫዋችነት ጥብቅ ዲሲፕሊን በአሰልጣኞችና በቡድን አጋሮቹ ጭምር የተመሰከረለት ነው፡፡ ወደ ሀዋሳ ከነማ እንዲቀላቀል ያደረጉት አሰልጣኝ ከማል አህመድ፥ ሙሉጌታ ከራሱም አልፎ የቡድን አጋሮቹ ደመ ሞቃት በሚሆኑበት ጊዜ ሰከን እንዲሉ በመምከር የአምበልነት ሃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ ተጫዋች ስለመሆኑ መስክረዋል፡፡

ደደቢት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት አመት ክለቡን ሲቀላቀል በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት ውበቱ አባተ፤ ሙሉጌታ የትኛውም አሰልጣኝ በቡድኑ ውስጥ እንዲኖረው የሚመኘው አይነት ተጫዋች ነው ሲሉ ተመሳሳይ አድናቆት ችረውታል፡፡

ራሱን የሚጠብቅ ፕሮፌሽናል ተጫዋች መሆኑ ለበርካታ አመታት አቋሙን ጠብቆ ለመዝለቅ እንዳስቻለውና ይህም ለብዙ ተጫዋቾች አርዓያ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ውበቱ ገልጸው ነበር፡፡

ሙሉጌታ ጫማውን ከሰቀለ በኋላም በእግር ኳስ ውስጥ የመቀጠል እቅድ ስለነበረው ገና ተጫዋች በነበረበት ወቅት ነበር የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን የወሰደው፡፡

ሙሉጌታ ምህረት ሀዋሳ ከተማን፣ ወልቂጤ ከተማንና ሀዲያ ሆሳዕናን በዋና አሰልጣኝነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ምክትል በመሆን አገልግሏል።

በአሁኑ ወቅትም ዳግም የቀድሞ ክለቡን ሀዋሳ ከተማን በአሰልጣኝነት በመምራት ላይ ይገኛል።

በኃይለማርያም ተገኝ