Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራን ለማሳደግ እየሠራሁ ነው- ፌዴሬሽኑ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፀረ አበረታች ቅመሞች ላይ አሠራሩን ለማዘመን እና ምርመራዎችን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ለዚህም ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በመተባበር አትሌቶች ባሉበት ሆነው እንዲሁም በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ኮሚቴ በማቋቋም ለአትሌቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለያየ አካባቢ ልምምድ ለሚሠሩ አትሌቶችም ስለ አበረታች ቅመሞች ግንዛቤ እንዲኖራቸው እያደረግን ነው ሲሉ በፌዴሬሽኑ የፀረ አበረታች ቅመሞች ተጠሪ ቅድስት ታደሠ ተናግረዋል፡፡

አትሌቶች ማንኛውንም መድኃኒት ከመውሰዳቸው በፊት ባለሙያዎችን ማማከር እንዳለባቸውም ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

የፀረ አበረታች ቅመሞች ላቦራቶሪ እንዲኖር እና ምርመራውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመርም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ አባል ሆነን ለመቀጠል እና አትሌቶችም ምርመራቸውን በአግባቡ እንዲያደርጉ፤ ምርመራዎችን የማብዛት እና አትሌቶችን የመከታተል ሥራ እያከናወንን ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የግል ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ምርመራውን እንዲያደርጉ ፌዴሬሽኑ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version