የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍራሽ ኃይሎችን እኩይ ተግባር በእውነትና በእውቀት መመከት ይገባል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

April 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍራሽ ሀይሎችን እኩይ ተግባር በእውነትና በእውቀት መመከት ይገባል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የድህረ እውነት ዘመን በእውነትና በእውቀት በሚል መሪ ሃሳብ ለሲዳማ ክልል የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠና  በሀዋሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በስልጠና መድረኩ ንግግር ያደረጉት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)÷ በሕዝቦች መካከል አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ታሪካዊና ትርክታዊ ትስስር በመጠናከሩ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እያረገች ትገኛለች ብለዋል፡፡

አፍራሽ ሃይሎች ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችን በመጠቀም የህዝቡን አንድነትና ወንድማማችነት ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው÷ የእነዚህን ኃይሎች እኩይ ተግባር በእውነትና በእውቀት መመከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አመራሩና ባለሙያዎች የድህረ እውነት ዘመንን በመረዳትና እውነትና እውቀት በመጨበጥ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና አገር ለማፍረስ በውስጥና በውጭ ኃይሎች የሚቀነባበሩ የሀሰት መረጃዎችን መመከት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የፓርቲው መረጃ ያመለክታል፡፡