አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህልና ስፖርት ሴክተር ማኅበረሰብንና የወል ትርክትን ለመገንባት የጎላ ሚና አለው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ገለፁ፡፡
“ትጋት ለስኬት መሰረት ነው” በሚል መሪ ሐሳብ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት፤ የባህልና ስፖርት ሴክተር ማኅበረሰብን ብሎም የወል ትርክትን ለመገንባትና የኢትዮጵያውያን አብሮነት ለማፅናት የጎላ ሚና እንዳለው በመገንዘብ መንግሥት ትኩረት እንደሰጠው ገልጸዋል፡፡
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበብና ባህል ፌስቲቫል ለኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ አስገኝቷል ብለዋል፡፡
በስፖርት ዘርፍም የስፖርት ቱሪዝምን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የባህልና ስፖርት ዘርፍ በሕዝቦች አብሮነትና ግንባታ ላይ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ዐቅም እንዳለው ያስገነዘቡት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ናቸው፡፡