አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተፈጥሮ ጸጋዎችን ይበልጥ በማስተዋወቅ የማክሮ ኢኮኖሚ ትሩፋት ተጠቃሚነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዲሁም የሚኒስቴሩ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበትያለፉት 9 ወራት አፈጻጸም ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩም ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ከዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ሁኔታ አንጻር እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉ ካስመዘገባቸው ውጤቶች ጋር በማስተሳሰር ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በዚህም በሁሉም ደረጃ ውጤታማ አፈጻጸም እንደተመዘገበ መገለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተለይም የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመዘርጋት በነበረው ርብርብ የዋጋ ግሽበትን ቢያንስ ባለበት ደረጃ እንዲቀጥል ማድረግ መቻሉ ነው የተጠቆመው፡፡
የኤክስፖርት መጠንን በመጨመር እና የውጭ ምንዛሪ ክምችትን በማሳደግ ፣ ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፉ ስኬታማ አፈጻጸም መመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡