አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአገልግሎት ውጪ የነበረውን የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አውሮፕላን ተጠግኖ ዳግም ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉ ተገለፀ።
አውሮፕላኑን ከተጣለበት ጥሻ አንስቶ በማደስ ከ37 ዓመታት በኋላ የበረራ አገልግሎት እንዲሠጥ ማድረግ መቻሉን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህም በሁሉም መስክ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልፀዋል።
አውሮፕላኑ አሥፈላጊውን ጥገና አግኝቶ መብረር እና ወደ ኃይል መመለስ እንዲችል በሰጠነው መመሪያ መሠረት ለተሳተፋችሁ የአየር ኃይል አመራሮች፣ ቴክኒሺያኖች፣ የመከላከያ ድጋፍ ሰጪ ሁሉ አመሠግናለሁ ብለዋል፡፡
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው በሰው ኃይል ግንባታ፣ ትጥቆችን ማሣደግና ከዘመኑ ዐቅም ላይ ማድረስ፣ መሠረተ ልማቶችን ተቋሙን በሚመጥን ልክ ማሥፋፋት ትኩረት የተሠጠባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አውሮፕላኑን ጠግኖ ወደ ኃይል መመለስም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል።
ዳሽ ፋይፍ (ቡፋሎ) በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን ይህን አውሮፕላን ለመጠገን ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ መውሰዱ ተገልጿል፡፡
ለትራንስፖርት፣ ለፓራሹት ዝላይ እና የካርጎ አገልግሎት መሥጠት የሚችል መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡