አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በማኅበራዊ ዘርፍ ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምታስቀጥል አስታወቀች፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ከሆኑት ቸን ሃይ እና ልዑካቸው ጋር በማኅበራዊ ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት፤ በሂደት ላይ ያሉና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ዋና ዋና የአጋርነት ሥራዎችን በይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በተለይም በቻይና ብሔራዊ የገጠር ልማት ፋውንዴሽን በኩል ለማኅበራዊ ጥበቃ ለሚደረገው ድጋፍ ሚኒስትሯ አመሥግነዋል፡፡
በቀጣይም የቻይና ኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ቀደም ሲል የተጀመረው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት አግባብ፣ ከሆናን ፕሮቪንስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ጋር የተፈረመው የመግባባቢያ ሰነድ አተገባበር እንዲሁም ከቻይና ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በሂደት ላይ ያለውን የሥነ-ልቦና እና የአካል ጉዳተኝነት ፈጠራ ላቦራቶሪ የመግባቢያ ሰነድ ማጠናቀቅ በሚቻልበት አግባብ ላይም ተወያይተዋል።
አምባሳደሩ በበኩላቸው ቻይና ለማኅበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጥ ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፋ ያላትን አጋርነት እንደምታስቀጥልና ድጋፏ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመጪው ነሐሴ በሚካሄደው የወጣቶች ፎረም ላይ ሚኒስትሯ እንዲገኙ ጋብዘዋል፡፡