አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሻሻል ሚዲያዎች በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱና ለሀገር ግንባታ የሚኖራቸውን ድርሻ ይበልጥ ከፍ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 25ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
የተሻሻሉት የአዋጁ ንዑስ አንቀጾች ላይ የምክር ቤት አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የአዋጁ መሻሻል መገናኛ ብዙሃኑን በማጠናከር ገለልተኝነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግስት የተቋማት ገለልተኝነት ላይ የሰራቸው ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ባለፉት ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ መንግስት ያደረጋቸው ማሻሻያዎች በሀገሪቱ ያለው ሚዲያ በአይነት፣ በስፋትና በተደራሽነት መጨመሩን ተናግረዋል።
ለአብነትም በሀገሪቱ ከለውጡ በፊት 122 የነበረው የሚዲያ ቁጥር ከለውጡ ወዲህ ወደ 272 ከፍ ማለቱንም አንስተዋል።
25 ብቻ የነበረው ቴሌቪዥን ወደ 103፣ 52 የነበረው ሬዲዮ ወደ 125 ማደጉን እና ሚዲያዎች ከሚጠቀሟቸው ቋንቋዎች አንጻርም ከ29 ወደ 60 ከፍ ማለቱን አስታውሰዋል።
አክለውም የአዋጁ መሻሻል እነዚህ ሚዲያዎች በሃላፊነት እንዲንቀሳቀሱና ለሀገር ግንባታ የሚኖራቸውን ድርሻ ይበልጥ ከፍ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ተሻሽሎ አዋጅ 1374/2017 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
በታሪኩ ለገሰ