የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በሠላምና ደህንነት ዘርፎች በትብብር ለመስራት መከሩ

By Melaku Gedif

April 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን የሀገር ውስጥና አደንዛዥ እፅ ቁጥጥር ሚኒስትር ሰይድ ሞሀሲን ናክቪ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የሀገራቱን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር)÷በአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ መደበኛ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ድምፅ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧን አንስተዋል፡፡

ይህም ሀገሪቱ በአፍሪካ አህጉር ለሰላም፣ ለፀጥታና ለልማት ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና እንደሆነ ጠቁመው÷ በቀጣይ ኢትዮጵያ በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አብራርተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 መካከል ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ቁልፍ መገለጫ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ÷ ኢትዮጵያ በክልሉ የሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ በመሳተፍ ይህንን ግብ ለማሳካት ቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚንቀሣቀሱትን እንደ አልሸባብ እና ሌሎች ቡድኖችን መዋጋት ቅድሚያ የሚሠጠው ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

ሀገራቱ በቀጣይ በሕገ-ወጥ የሠው፣ መሣሪያ፣ ዕፅ፣ ዝውውሮች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ እንዲሁም በፀረ-ሽብርተኝነት ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በፓኪስታን ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የፓኪስታን መንግስት ለሚያደርገው ከፍተኛ አስተዋፅኦም አመስግነዋል፡፡

ሰይድ ሞሀሲን ናክቪ በበኩላቸው÷ ኤምባሲው ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን የሚያደርገውን በረራ ማስጀመሩን ጨምሮ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ የተደረገውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

ሁለቱ ወገኖች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሕግ አስከባሪ በተለይም በፌደራል ፖሊስ ስልጠና እና ልምድ ልውውጥ ለማጠናከር ማስማማታቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡