Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጸሎተ ሐሙስ – ምስጢረ ቁርባን የተገለጠበት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ትኅትናን፣ ፍቅርን፣ መታዘዝን እና ዝቅ ማለትን ያስተማረበት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የሰሙነ ሕማማት አራተኛው ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ነው፡፡ ዕለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የበላበት እና እግራቸውን በትሕትና ያጠበበት ነው፡፡

ቀኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ እንደየሃይማኖቱ አስተምኅሮዎች በተለያዩ ሥርዓቶች ይታሰባል፡፡

የሰሙነ ሕማማት 4ኛው ቀን ጸሎተ ሐሙስ፤ ርኩሰትን የሚቀድስ፣ ያደፈ ማንነትን የሚለውጥ ቅዱስ ቁርባን የተሰጠበት ዕለት መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል መምህራን ይገልጻሉ፡፡

ዕለቱ በተለያዩ ስያሜዎች ማለትም፤ “ጸሎተ ሐሙስ”፣ “ትእዛዘ ሐሙስ”፣ “ሥርዓተ ሐሙስ (የምስጢር ቀን)”፣ ህፅበተ ሐሙስ፣ “የሀዲስ ኪዳን ሐሙስ” እና “የነጻነት ሐሙስ” በመባል እንደሚከበር መምህራኑ ያስረዳሉ፡፡

እንደመምህራኑ ማብራሪያ “ጸሎተ ሐሙስ” መባሉ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ረጅሙን ጸሎት ያደረገበትና ቅዳሴም የቀደሰበት፤ ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 የሚገኘውን ረዥም ጸሎት የጸለየበት በመሆኑ ነው፡፡

“ትእዛዘ ሐሙስ” መባሉም፤ “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” (ዮሐ.13:15) እንዲሁም “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ.15:34) ብሎ አዲስ ትእዛዛትን የሰጠበት ቀን ስለሆነ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

እንዲሁም “ሥርዓተ ሐሙስ” (የምስጢር ቀን) የተባለው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ስጋ እና ደም እራሱ ፈትቶ የሰጠበት ሚስጢረ ቁርባን የተሰጠበት በመሆኑ፤ ሥርዓተ ሕጽበትን (ትሕትናን) እና ሥርዓተ ቁርባንን የመሠረተበትና ያስተማረበት ስለሆነ ነው ይላሉ መምህራኑ፡፡

በሌላ በኩል የሀዲስ ኪዳን ሐሙስ የተባለው፤ ሀዲስ ኪዳን የተጀመረባት ሐሙስ መሆኗን ለማውሳት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

በተጨማሪም “የነጻነት ሐሙስ” የሚባለው፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው የሚሉት መምህራኑ፤ እንደ ሐይማኖቱ አስተምኅሮ በጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓልአዛር ቤት ከሐዋርያት ጋር ለማዕድ መቅረቡን ያነሳሉ፡፡

ጸሎተ ሐሙስ ለአማኞች ሕይወት የቅድስና እና የሕዳሴ ቀን መሆኑን በመግለጽ፤ ይህም ምስጢረ ቁርባን የተገለጠበት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ትኅትናን፣ ፍቅርን፣ መታዘዝን እና ዝቅ ማለትን ያስተማረበት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም ኃጢአትን የሚያስተሠርይ፣ ርኩሰትን የሚቀድስ፣ ያደፈ ማንነትን የሚለውጥ ቅዱስ ቁርባን የተሰጠበት ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ቂጣ እና ጉልባን ይበላል፤ ይህም እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን እና ለጊዜው ቶሎ የሚደርሰው ምግብ በመሆኑ ያንን እንደሚበሉ የሚያወሳ ነው፡፡

የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣም ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፤ ይህም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ሁሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ያለመ መሆኑን መምህራን ያብራራሉ፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version