አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2017 ሀገራዊና የዘርፉ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በየዘርፉ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን አንስተው÷ በቀጣይም ኅብረተሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሁሉም ሚናውን በመገንዘብና የተሰጡትን ተልዕኮዎች ከሀገራዊ እቅዱ ጋር በማስተሳሰር በላቀ ትጋት መስራት፣ የመንግስትን ጥረት መደገፍና ለስኬታማነቱ መተባበር እንዳለበት ገልጸዋል።
በዘርፉ የመረጃ ችግርን ለመፍታት የሚያስችል ውጤታማ የዲጂታል ስርዓት ለመዘርጋት በቅንጅት እንደሚሰራ አንስተዋል።
ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለገጠር ልማት ስራዎች እንዲሁም ለሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊነትና ስኬታማነት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።