አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሀገራዊ አፈጻጸም ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራር እና ሠራተኞች ተወያይተዋል፡፡
በመድረኩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ የለውጡ መንግሥት ኃላፊነት የተረከበበት ወቅትና ቀጣዮቹ ዓመታት ድርቅ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ግጭት እና ሌሎችም ከባድ ፈተናዎች የነበሩባቸው ቢሆኑም ብስለት በተሞላበት አመራር መሻገር መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
የበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በሁሉም መስኮች ጉልህ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ ስኬቶችን አጉልቶ ማሳየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለመድረኩ ያቀረቡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ወደተሟላ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ሲገባ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች በመጠናታቸው እና በብስለት በመመራቱ የላቀ አፈጻጸም ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ሲተገበር አጠቃላይ የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር፣ የኢንቨስትመንት እና ንግድ ከባቢን ለማሻሻል፣ የዘርፎችን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና የመንግሥትን የማስፈጸም ዐቅም ለማጎልበት ታሳቢ ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል።
የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ ብዝኃ-ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማረጋገጥ፣ የመንግሥትን ገቢ የመሰብሰብ ዐቅም በማሳደግ፣ የወርቅና ሌሎችም የማዕድን ሀብቶችን ወደ ሕጋዊ የግብይት ሥርዐት በማስገባት የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በማድረግ፣ የኃይል መሠረተ ልማቶችንና የመስኖ አውታሮችን ግንባታ በማፋጠን ረገድ አፈጻጸሙ ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።
ካለው ዓለም አቀፋዊ የንግድ ሥርዓት ሁኔታ እና አዝማሚያ አንጻር ምቹ ዓውዶችን በመመልከት በገቢር ነበብ የኢትዮጵያ ትልሞች በበጀት ዓመቱ ለማሳካት የታቀዱ ተግባራትን በቀሪዉ ሩብ ዓመት በላቀ ተነሣሽነት መፈጸም እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል።