አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መጪው የስቅለትና የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ለፀጥታ አካላት አመራሮች የበዓል ቅድመ ዝግጅቱን አስመልክቶ የስራ መመሪያ ተሰጥቷል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት በተገኙበት የስቅለት እና የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ወደ ስራ ተገብቷል።
የፀጥታ አካላት የህዝብን አቅም በሚገባ በመጠቀማቸው እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው ከዚህ ቀደም የተከበሩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በሠላም መከበራቸው የተገለፀ ሲሆን÷ ከበዓላቱ አከባበር መልካም ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ውጤቶች መገኘታቸው ተመላክቷል።
የስቅለትና የትንሣኤ በዓላት ሰሞን ሊከሰቱ የሚችሉ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ማጭበርበሮች እንዲሁም ሽማቹ በሚጠቀማቸው የምግብ ተዋፅኦዎች ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅለው ወደ ገበያ ይዘው የሚወጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ በግብይት ወቅት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት ተላልፏል።
በአብያተ ክርስቲያናትና በገበያ ስፍራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ ህግ የማስከበር ስራ ከመስራት ባሻገር ተገቢነት የሌለውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።
በበዓል ሰሞን ሊከሰቱ የሚችሉ የወንጀልና ትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተለይም አልኮል ጠጥተው የሚያሽከረክሩና የተለያዩ የደምብ መተላለፍ ጥፋቶችን ለመከላከል በተጠኑ የከተማዋ አካባቢዎች ተገቢው የቁጥጥርና የፍተሻ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል።
ህብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ትስስር አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም የፀጥታ አካላት አመራሮችና አባላት በጥብቅ ዲስፕሊን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጌቱ አርጋው እና የከተማ አስተዳደሩ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ጥብቅ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።