የሀገር ውስጥ ዜና

የፖሊስ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች አጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ሁኔታን በጋራ ገመገሙ

By Adimasu Aragawu

April 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች አጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ሁኔታን ገምግመዋል።

በመድረኩ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን አፈና በማካሄድ የግድያ ወንጀል የሚፈፅሙ እና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

በመኪና ስርቆት፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ እና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ በህገ-ወጥ መድሃኒቶች ዝውውር፣ በሞባይል ስርቆት፣ በተሽከርካሪ ስፖኪዮ፣ ጎማና በሌሎች የመኪና መለዋወጫዎች ስርቆት የተጠረጠሩ ከኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተመላክቷል።

በኦፕሬሽኑ የከተማው ሰላምና ደኅንነት የበለጠ እንደተረጋገጠና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ መሆኑ በግምገማው ላይ መገለጹን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።

በቀጣይም ኅብረተሰቡን ባማረሩ ወንጀሎች ላይ የሚካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንዲቀጠልና የእርስ በእርስ ቅንጅትን የበለጠ ማጠናከር፣ የጥበቃና ፍተሻ አቅምን ማሳደግ፣ ማኅበረሰብ የፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር፣ የሕዝባዊ ሠራዊት ተሳታፊዎችን በማሳደግ በጋራ መስራት እና የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡