Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሀረር ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት የተከማቸ ከ10 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀረር ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት በህገወጥ መንገድ የተከማቸ ከ10 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀረሪ ክልል ፖሊስ አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ጣሰው ቻለው በክልሉ ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቆም በተሰራው ስራ በአንድ ግለሰብ ቤት ተከማችቶ የተገኘ ከ10 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

ነዳጁ የተያዘው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በህገ ወጥ መንገድ በቤት ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ ነው ብለዋል።

ነዳጅን በጄሪካን እና በሀይላንድ በህገ ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤታቸው ደብቀው የተገኙት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡም በአካባቢው ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኝ የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version