አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ አቅዳ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬይትናም 2025 ፒ4ጂ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተግባራዊ እያደረገቻቸው የሚገኙ ኢኒሼቲቮችና ፖሊሲዎችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
በዚህም 4ኛው የፒ 4ጂ ፕሮጀክት ጉባዔ የአረንጓዴ ልማትን ለመገንባት፣ በኢኖቬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማፋጠን እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል፡፡
በጉባዔው መንግስት፣ የግል ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት የአረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ ያደረጉትን ጥረት እንደተመለከቱ ገልፀው÷ይህም ትናንሽ ፕሮጀክቶች ከተባበሩ በአረንጓዴ ልማት ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ 4ጂ ጉባዔ ለማዘጋጀት ችቦ መረከቧን ጠቅሰው ÷ ጉባዔው በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ በማይበገር ግብርና እንዲሁም በወጣቶችና ሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት አንዷ መሆኗን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስተሩ÷የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድም በርካታ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ ያደረገች ግንባር ቀደም ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአጀንዳ 2030 እና አፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር በማጣጣም በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመግንባት አቅዳ እየሰራች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስቀመጠችውን እቅድ ለማሳካትም፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ ማድረጓን እንዲሁም የታዳሽ ሃይል አማራጮች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አንድ ሀገር ብቻውን የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የአረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ የጋራ ትብርብር እና ፈጣን ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፒ 4ጂ ትብብር ጉባዔ አባል እና መስራች እንደመሆኗ የአባል ሀገራቱ የጋራ ግቦች እውን እንዲሆኑ እንዲሁም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጉባዔውን በተሳካ ሁኔታ ላካሄደችው ቬይትናም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ