Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቬይትናም ይፋዊ ጉብኝት በተለያዩ ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር የሚያግዙ ስምምነቶች ተደርገዋል – ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቬይትናም ይፋዊ ጉብኝት ወቅት በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ስምምነቶች መደረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በቬይትናም የተደረገውን ይፋዊ ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷የኢትዮጵያና ቬይትናም ግንኙነት 50 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው፤የኢትዮጵያ መሪ በከፍተኛ ልዑክ ደረጃ ጉብኝት ሲያደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።

በጉብኝቱ መሪዎቹ ስለ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲወያዩ፣ የተለያዩ ስምምነቶች እንዲፈፀሙ እና በቀጣይ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ምን አይነት አካሄድ መከተል እንደሚገባ ለመነጋገር ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቬይትናም በረራ እንዲጀምር የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ጠቁመው÷ ይህም በሀገራቱ መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ እና የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ስምምነቶች መደረጋቸውን እና አጠቃላይ የግንኙነቱን ማዕቀፍ በተመለከተ ወደ ስምምነት ለመግባት ንግግር መደረጉን ጠቅሰዋል።

ስምምነቶቹ ወደ ተግባር ሲገቡ ዘላቂነት ያለው እና ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ለማጠናከር ጥረት የሚደረግበት መድረክ የሆነውን ፒ4 ጂ የትብብር እና የጥምረት መድረክን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ የማሰናዳት ኃላፊነት መረከቧን ተናግረዋል።

ይህም በአካባቢ ጥበቃ እና በታዳሽ ሃይል ዘርፉ ላይ የተሰራውን ስራ ለዓለም ለማሳየት እንደሚጠቅም ገልጸው÷ ሌሎች ሀገራት ልምድ እንዲወስዱ እና የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ እንዲደግፉ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ኣመልክተዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version