Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን ንግድ ሚኒስትር ጃም ከማል ኻን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ እና ኢንቨትመንት ዘርፍ ትብብር ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) ÷በግንቦት ወር ኢትዮጵያ ስለምታዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት የንግድ ትርዒት እና ኢንቨስት ኢትዮጵያ የከፍተኛ ደረጃ ቢዝነስ ፎረምን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከግንቦት 15 እስከ 17 በአዲስ አበባ በሚካሄደው ፎረም ከ100 በላይ የሚሆኑ የፓኪስታን ታላላቅ ኩባንያዎች የሚሣተፉበት የፓኪስታን የነጠላ ሀገር የንግድ ትርዒት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡

የንግድ ትርዒቱ እምቅ የኢኮኖሚ እና አምራች ኃይል ያላቸውን ሁለቱን ሀገራት በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

ጃም ከማል ኻን በበኩላቸው ÷የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት እንድታስመዘግብ የሚያደርገውን የአመራር ብስለት አድንቀዋል፡፡

በቀጣይ ወር ሚኒስትሩን ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመራው የፓኪስታን ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የንግድ ማህበረሠብ ልዑክ ከፍተኛ ልምድ እንደሚቀስም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ሁለቱ ወገኖች የሀገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version