Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመተሳሰብ ያለንን ተካፍሎ የመኖር ባሕላችንን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብርን ባሕል ማድረግ እና ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው ሕጻናት ማዕድ አጋርተዋል።

በዚህ ወቅትም የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብርን ባሕል በማድረግ እና ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዓል ሲመጣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ይቸገራሉ፤ “ልጆቻችንን ምን እናበላለን፣ ልጆቻችን የሠው እጅ ያያሉ” በሚል እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ልጆች ሲመኙ አይታ ማጉረስ የተሳናት እናት ብዙ ትታመማለች፤ ውስጧ ይደማል፤ ይህን የእናቶች እንባ በማዕድ ማጋራት ማበስ መቻል ደግሞ ትልቅ ሀሴት ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በአንጻሩ ሃብታሞች ተርፏቸው ይደፋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ተርፎ ከሚደፋ ተሳስበን፣ ያለንን ተካፍለን የመኖር ልማድን እንደ ሀገር ማዳበር ይጠበቅባናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለራሷ በቂ የሆነ ምርት እንደምታመርት ጠቁመው÷ ችግሩ ምርት ሳይሆን የተገኘውን ተሳስቦና ተካፍሎ መጠቀም ላይ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የማዕድ ማጋራት በየመስሪያ ቤቱ፣ በየአካባቢውና በየጎረቤቱ የሁላችን ልማድ ሲሆን ለተቸገሩ ዜጎች የዕለት ጉርስ ሃሳብ አይሆንም ነበር ነው ያሉት፡፡

ስለሆነም ሁሉም ዜጋ በዓሉን ሲያከበር አቅም ለሌላቸው ዜጎች ያለውን በማጋራትና አብሮነቱን በማሳየት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ መልኩ መልካምነትን እና ደግነትነን ማባዛት ለቀጣዩ ትውልድ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሱት፡፡

በሌላ በኩል የበዛ መስገብገብ እና እኔ ብቻ ልጠቀም የሚሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች መበራከት ነባሩ የኢትዮጵያ የመተሳሰብ ባህል በመሸርሸሩ የመጣ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version