የሀገር ውስጥ ዜና

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቬይትናም ቆይታ ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

April 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬይትናም የነበራቸው ጉብኝት ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የቬይትናም ጉብኝት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ቆይታ መሆኑን ገልጸዋል።

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ቆይታ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በቬይትናም የነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት የተሳካና ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው። ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካል ነባራዊ ሁኔታና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከአሁናዊ የብልፅግና እይታና ፕራግማቲክ ጉዞዋ የሚቀዳ የስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በያዝነው ሳምንት ለይፋዊ መንግስታዊ ጉብኝት ወደ ቬይትናም አቅንተው ነበር። ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1976 ወዲህ በሀገር መሪ ደረጃ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ላለፉት 50 ዓመት ያህል በመሪዎች ደረጃ ያልነበረውን ግንኙነት የቀየረ እጥፋት ሆኗል። በዚህም ምክንያት ቬይትናም በመሪዋ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህን የቆየ ወዳጅነትና ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚያጠናክር፣ የመሪያችንንና የህዝባቸውን ክብር የሚመጥን እጅግ የደመቀ አቀባበል አድርጋላቸዋለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ በቆይታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ከሆነው የቬይትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም ብዝሃ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ የሰከነ እና ጥልቀት ያላቸው ውይይቶችን አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው፣ ከሀገሪቱ ቁልፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋርም የመወያየት እድል አግኝተዋል፡፡ የሮቦቲክ እና ሃይቴክ ኢንዱስትሪዎችንም ጎብኝቷል፡፡ ኦሽን ፓርክ በመባል የሚታወቀውን በሀገር በቀል ኩባንያ የሚለማ የከተማ ግንባታ ስራዎችንም ተመልክቷል፡፡

በሁለትዮሽ እና ብዝሃ ግንኙነቶች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ከመደረጉም በላይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሰው ሀብት ልማት እና አቪዬሽን ኢንዱስትሪ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነቶች ፈርመዋል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ልዑኩ፣ አጋርነት ለዕድገት እና ልማት (P4G) ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን ልምድና ተሞክሮ አካፍሏል፡፡

የደቡብ ምስራቅ እስያ አካል የሆነችው ቬየትናም ከቀጣናው ሀገራት እጅግ በመዘግየት ማለትም በ1986 በሯን ለዓለም የከፈተችና የኢኮኖሚ ሪፎርሟን የጀመረች አገር ናት፡፡ ለሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚና ፈጣን እድገት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የኢኮኖሚ ሪፎርሟ ዶይ ሞይ (Đổi Mới) ወይም Economic renovation through opening up በመባል የሚታወቅ ነው፡፡

ቬይትናም የኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ በጠንካራ ፓርቲ የሚመራ ጠንካራ መንግስት በመገንባቷ ባለፉት 30 ዓመታት እጅግ አስደናቂ የሚባል የኢኮኖሚ እድገትና ማህበራዊ ለውጥ ያስመዘገበች ሀገር ናት፡፡ ከ1990ዎቹ በፊት እጅግ ደሃ ከሚባሉ ሀገራት ታርታ ተሰላፊ የነበረች ሲሆን፣ ከነበረችበት እጅግ ጥልቅ የሆነ ድህነት ተነስታ በአንድ ትውልድ ብቻ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ የቻለች ሀገር ናት፡፡

ቬይትናም ዛሬ በምግብ ሰብል ራሷን ከመቻል አልፋ በቀጣናው በግብርና ምርቶች በተለይም በሩዝ፣ በቡና፣ ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶች ግምባር ቀደም ላኪ ሀገር መሆን ችላለች፡፡ የከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል በመፍጠር በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ የኤሌክትሮኒክስ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የመጫሚያ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ኤክስፖርት ከሚያደርጉ አገሮች ተርታ የምትሰለፍ ናት፡፡

በጠንካራ ፓርቲ የሚመራው የቬይትናም ጠንካራ መንግስታዊ ቢሮክራሲ፣ ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ በተለይም ለግብርና ልማት እና ኤክስፖርት መር አምራች ኢንዱስትሪዋ ስኬታማነት የላቀ አበርክቶ አለው፤ ሀገሪቱ በዚህ እይታ በአለም አቀፍ ደረጃና በቀጠናው ለነጻ የንግድ ስምምነቶች እና ዝቅተኛ ታሪፍ እንዲሁም በክህሎትና እውቀቱ የበለፀገ የሰው ኃይል ልማት የሰጠችው ትኩረት ለኢኮኖሚ እድገቷና ልማቷ ውጤታማነት መሰረት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋዊ ጉብኝትም ሀገራችን የጀመረችውን የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ስራዎችን የሚያጠናክሩ፣ የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያጎለብቱ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያሳልጡ ልምዶች መቅሰም አስችሏል፡፡ የተገኙ ልምዶችና ተሞክሮዎችንም ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ተሞክሮ 1፣

ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠትና በፅናት የታገዘ እልህ አስጨራሽ ርብርብ በማድረግ በአንድ ትውልድ የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ብቻ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መዝገብ የሚቻል መሆኑን ከቬይትናም የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ቬይትናሞች ለግብርና ልማት፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለሰው ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቶችን በማድረግ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበዋል፤ በዚሁ ባለፉት 30 ዓመታት ከ5-7 በመቶ ያልተቋረጠ እድገት በማስመዝገብ አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገትን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በአንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ብዝሃ ሴክተር የኢኮኖሚ ግንባታ ተሸጋግራለች፡፡ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ እቅዷና ሪፎርሟ ግብርናን፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ግንባታዋ አዕማድ ወይም ምሳሶ በማድረግ ባለፉት 7 ተከታታይ ዓመታት ከ7 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት በማረጋገጥ ታሪካዊ ስራ አከናውናለች፡፡

ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷንም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡ የቬይየትናሞቹ ልምድና ተሞክሮም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ አቅጣጫ ትክክለኛነትን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከቬይትናም የተገኘው ልምድና ተሞክሮ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሪፎርም በማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር በያዘችው መንገድ ከቀጠለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቬይትናም ካስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የላቀ እድገት ማስመዝገብ እንደምትችል የሚጠቁም ነው፡፡

ተሞክሮ 2፣

ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የቬይትናም ዜጎች በ1990ዎቹ ዓመታት ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ ነበር። ሆኖም ቬይትናም በተከተለችው የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ በተለይም ለግብርና ልማት በሰጠቸው ልዩ ትኩረት በ2020 ይህን አኃዝ ወደ 4 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጋለች፡፡ የግብርና ሪፎርሟ ውጤታማ በመሆኑ ራሷን በምግብ ሰብል ከመቻል አልፋ በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀጣናው ከፍተኛ ላኪ ሀገር ሆናለች::

ይህ በጎ ልምድና ተሞክሮም፣ ኢትዮጵያ ተረጅነትን በመቀነስ፣ ራስን በምግብ ሰብል በመቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገችው ላለው ሁለንተናዊ ጥረት በእጅጉ ጠቃሚ አስረጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ አብዮት ራስን ለመቻል ያደረገችው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሆኗል፡፡ ከዚህ የተገኘውን ልምድ በመውሰድ አሁን ደግሞ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በሩዝ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ጀምራለች፡፡ በዚህም ረገድ የቬይትናሞች ስኬት ኢትዮጵያ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኗን ከማረጋገጥ ባለፈ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡

በመሆኑም የጀመርናቸውን መልካም ስራዎች የሚያጠናክሩ የአገር ውስጥ ልምዶችን ከማጎልበት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ በጎ ልምዶች በመቀመር በግብርና ዘርፍ የተጀመረውን መነሳሳት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቬየትናም ያሉ በግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ የሆኑ አገሮች ኢትዮጵያ ለምትካሂዳቸው የሪፎርም ስራዎች ጥሩ መነሻ ሆኖ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

ተሞክሮ 3፣

ቬይትናም የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ በቀጣናው ካሉ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ድርጅቶች ጋር በነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ዙሪያ ሰፋፊ ድርድሮችን አካሂዳለች፡፡ በዚህም ረገድ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በየዓመቱ ከ34 ቢሊየን ዶላር በላይ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡ በተለይም እንደ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ችላለች፡፡ ይህም በቀጣናው ከፍተኛ የሚባል የኢንቨስትመን ስበት ማሳያ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ጋር ብዙ ርቀት የተጓዘ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ድርድሮቹም ውጤት እየተገኘባቸው መጥቷል፡፡ በምስራቅ አፍሪካም ነፃ የንግድ ስምምነት ለመፍጠር ከሀገሮቹ ጋር በርካታ ድርጅሮችን እያካሄደች ነው፡፡ ይህም ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

በአፍሪካ ህብረት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ስራ እያከናወነች ነው፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠና ድርድር በማካሄድ ቬየትናምን ሰፊና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንድታገኝ ያስቻሏትን የድርድር መንገዶች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን በመመርመር ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ ለምትፈጽማቸው ስራዎች እንደየሁኔታው መጠቀም ይገባል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቬየትናም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ እየተጋረጠባቸው መጥቷል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ታሪፍ፣ ታዳሽ የሃይል አቅርቦት፣ የሰው ሃይል ፣ እየዘመነ የመጣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአንድ ማዕከል ወይም አካባቢ የተሰበሰቡ ኢንዱስትሪዎች መጠናከር እና የነጻ የንግድ እና ኢኮኖሚ ዞኖች መፈጠር እንደ ቬይትናም ላሉ ሀገሮችና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝት ከዚህ አኳያ ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ይህን ምቹ እድል አጠናክሮ መጠቀም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ተሞክሮ 4፣

ቬይትናሞች ለሰብአዊ ልማት በተለይም ደግሞ ለቴክኒክና ሙያ የሰጡት ልዩ ትኩረት ኢኮኖሚያቸው ይበልጥ እንዲያድግ ረድቷል፡፡የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅባለቸው ከ99 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅበላውም ወደ ዘጠና በመቶ የተጠጋ ነው፡፡ ይህ አሃዝ በመካከለኛ እድገት ደረጃ ካሉት ሀገሮች ከፍተኛው ነው፡፡ ቬይትናም በዓለም አቀፉ የሰብአዊ ልማት index መሰረት ከሲንጋፖር ቀጥላ ሁለተኛዋ የሰብአዊ ካፒታል የገነባች ሀገር ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያም በቅርቡ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የትውልድ ግንባታ አቅጣጫን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝትም ከዚህ አኳያ ጠቃሚ ልምድ የተገኘበት ነው፡፡ ቬይትናሞች የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ሀብት ልማት ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በየዓመቱ መጠነኛ ቁጥር ላላቸው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ለመስጠት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አብሮ ለመስራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ይህንኑም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬይትናም የነበራቸው ቆይታ ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው። የልዑኩም ቆይታ የኢትዮጵያን ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ተሞክሮ ለመቃኘትና የጉዞአችንን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ባለፈ መጪው ጊዜ አዲስ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት እንዲሆን አቅም የፈጠረ ነው።

በቬይትናም የቆይታ ምዕራፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የታደሙበት “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የቬይትናሙ የፒ4ጂ ጉባኤ፣ ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ትልቅ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች የታዩበት መሆኑ ታይቷል። የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።

ጉባዔው ለ2027 ለሀገራችን ሌላ እድል አምጥቶና የመሪያችንንና ሕዝባችንን ክብር ባረጋገጠ አኳኋን ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ4ጂ ጉባዔ እንድታካሂድ ችቦ አረካክቧል። በመሆኑም ሀገራችን እንደ ቬይትናም በሌላ ምዕራፍ ልምድና ተሞክሮዋን፣ በብዝሃ እምርታና ስኬት ይዛ እንድትቀርብ ለማድረግ ርብርባችንን ከወዲሁ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል።