አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ለ461 ወገኖች ለትንሳዔ በዓል መዋያ ዛሬ ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉ የተደረገው ከተማ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ባሰባሰበው ከ18 ሚሊየን 300 ሺህ ብር በላይ እንደሆነ በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በወቅቱ እንደተናገሩት፥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በተለያዩ የልማት ስራዎች በማሳተፍ የማቋቋም ተግባር እየተከናወነ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ለእነዚህ ወገኖች በበዓላት ወቅት ማህበረሰቡን በማስተባበር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ከተማ አስተዳደሩ በበዓላት ወቅት ተካፍሎ የመብላትና የመተጋገዝ ባህል እንዲዳብር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፥ይህም ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያስችል ነው ብለዋል።